የቁልፍ መሰረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነትን መጠበቅ የሀገር ደኅንነትና ሉዓላዊነትን መጠበቅ ነው

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

የቁልፍ መሰረተ ልማቶችን የሳይበር ደህንነት መጠበቅ የሀገር ደኅንነትና ሉዓላዊነትን መጠበቅ እንደሆነ ተገለጸ፡፡ በ5ተኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር የመክፈቻ መርሃ ግብር ላይ “የቁልፍ መሰረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት ሀገራዊ ቁመና” በሚል ጭብጥ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡ በዚህ የፓናል ውይይት ላይ ከተለያዩ ቁልፍ የሀገራችን ተቋማት የተውጣጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ፓናሊስት ከሆኑት መካከል የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ም/ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ሲሳይ ቶላ በፓናል ውይይቱ ላይ እንደገለጹት "የሳይበር ጥቃት ከፍተኛ የሆነ ማሀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳቶችን ሊያደርስ ይችላል። እነዚህን ጥቃቶች ለመከላከል የጥበቃ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል። የጥበቃ ሥርዓቱ ደግሞ ሁሉን አቀፍ (holistic) መሆን አለበት። በተጨማሪም ቅንጅት እና ትብብር፣ በተለይም የባለድርሻ አካላት ቅንጅት እና ትብብር በእጀጉ ያስፈልገናል። ሰው ላይ መሥራትም ጥቃቶችን ለመከላከል ወሳኙ ጉዳይ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሌላው የውውይቱ ፓናሊስት የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ኢዮብ ገብረየሱስ ሲሆኑ፤ የፋይናንስ ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ አገልግሎቱ ከቴክኖሎጂ ጋር እየተቆራኘ በመምጣቱ ውስብስብና ከፍተኛ ለሆነ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም የፋይናንስ ዘርፉን የሳይበር ደህንነት ማረጋገጥ ጤናማ ለሆነ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሥርአት ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የፋይናንስ ተቋማት በኢኮኖሚው ውስጥ የማይተካ ሚና ያላቸው በመሆናቸው እና ሌሎች ተቋማትም ሥራቸውን የሚያከናውኑት የፋይናንስን ስርአቱን ተጠቅመው በመሆኑ እና አገልግሎቱም ዲጂታል እየሆነ በመምጣቱ የፋይናንስ ዘርፉን የሳይበር ደህንነት ማረጋገጥ አጠቃላይ ለማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ደህንነት መረጋገጥ ወሳኝ ነው ሲሉ አቶ ኢዮብ ገብረየሱስ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ሌላው የፓናል ውይይቱ ተሳታፊ ሲሆኑ፤ የቁልፍ መሠረተ ልማቶችን ደህንነት መጠበቅ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ሲያብራሩ፤ የቁልፍ መሰረተ ልማቶችን ደህንነት ሳናስጠብቅ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ አንችልም ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቁልፍ መሠረተ ልማቶቻችን ከሕብረተሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እና ሕይወት ጋር በእጅጉ የተሳሰሩ በመሆናቸው ደህንነቱ ባልተጠበቀ መሠረተ ልማት የምንሰጣቸው አገልግሎቶች ተዓማኒነት አይኖራቸውም፡፡ ከዚህ አኳያ በተለይም እንደ ኢትዮ ቴሌኮም "የኢትዮ ቴሌኮምን ደህንነት ማስጠበቅ የሀገርን ደህንነት ማስጠበቅ ነው" በሚል መርህ ላይ ተመስርተን እየሠራን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንግደ ግሩፕ ቺፍ ኢንፎርሜሽን ኦፊሰር አቶ ጌትነት ታደሰ በፓናል ውይይቱ ላይ የተሳተፉ ሌላው ፓናሊስት ሲሆኑ፤ የቁልፍ መሰረተ ልማቶቻችንን ደህንነት ለማስጠበቅ በትብብርና በቅንጅት መስራት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ የቁልፍ መሰረተ ልማቶችን ደህንነት ለማረጋገጥ መወሰድ ካለባቸው እርምጃዎች መካከል፤ ዘመኑን የዋጀና ደህንነቱ የተረጋገጥ ቴክኖሎጂ መጠቀም፣ ተቋማዊ የሳይበር ደህንነትን ለመምራት የሚያስችል የአሰራር ስርአት መዘርጋት፣ ብቁና የሳይበር ደህንነት ግንዛቤው ያደገ የሰው ሃይል መገንባት፣ ቀጣይነት ያለው የሳይበር ደህንነት ግንዛቤና ንቃተ ሕሊና ግንባታ ሥራ መስራት፣ እንዲሁም የሳይበር ጥቃት በሚከሰትበት ወቅት ጥቃቱን ፈጥኖ የማወቅና የመለየት እና ከጥቃቱ አገግሞ ወደነበረበት የመመለስ አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ አቶ ጌትነት ገልጸዋል፡፡

የፓናል ውይይቱን የመሩት የኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነት ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃኑ በየነ ሲሆኑ፤ ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀምና እርስ በእርሳቸው እየተሳሰሩ በመምጣት በከፍተኛ ደረጃ የዜጎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ እያቀለሉ መምጣታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ነገር ግን የቁልፍ መሠረተ ልማቶች ደህንነት ስጋቶችና ጥቃቶች በዓለም አቀፍ ደረጃና በሀገራችንም ከምንጊዜውም በላይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል። በመሆኑም በሀገራችን የቁልፍ መሰረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት ጉዳይ ላይ እንደዚህ አይነት ውይይትና ምክክር መካሄዱ የሀገራችንን የሳይበር ደህንነት ለመጠበቅና ዲጂታል ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ ትልቅ እርምጃ ነው ሲሉ ዶ/ር ብርሃኑ በየነ ገልጸዋል፡፡

Innehållspublicerare


የቅርብ ዜናዎች